top of page

Testimonials

ዶክተር አክሊሉ የዚህን መጽሐፍ ረቂቅ እንድመለከተው ሲልክልኝ፥ ሌላ የጀመርኩት ሥራ ስለነበረኝ ያንን ስጨርስ እመለከተዋለሁ ብየ ገፋ ከማድረጌ በፊት፥ ገጾቹን ማገላበጥ ጀመርኩ። ሥራየን ትቼ አንብቤ እስክጨርሰው ድረስ በዚያው ምርኮኛው ሆኜ ቀረሁ። ጣመኝ፥ ጣፈጠኝ። ዕውቀትን በማያደናቅፍ አማርኛ የማቅረብ ሀብት የተሰጣቸው ደራሲዎች ጥቂቶች ናቸው። አንዱ ዶክተር አክሊሉ ነው። 

ስለ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ብዙ ተጽፏል። ሐውልቶች ተቀርጸውላቸዋል፤ ድርጅቶች በስማቸው ተጠርተዋል። ዘላቂውን ታሪካቸውን የያዘው ግን፥ ይህ ዛሬ የምንመርቀው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ ነው። 

ሌሎቹ ሐውልቶች ሊፈርሱ ይችላሉ፤ ሲፈርሱም አይተናል። ትምህርት ያፈራውና የተጻፈው ታሪክ ግን፥ የማይፋቅ የማይሰረዝ ሐውልት ሆኖ ይኖራል። የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ አክሊሉ ያቆመላቸው ነፋስ፥ ቢነፍስ፥ ዝናም ቢዘንም፥ መሬት ቢንቀጠቀጥ የማይነቃነቅ ሐውልት ነው። 

የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ የሁለት ሥርዓተ ትምህርቶች ታሪክ ነው። “እኛ ምን ትምህርት አለን?” የሚል ሰው ሲያጋጥማችሁ፥ “የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲን ታሪክ አንብብ በሉት። ከውጪስ ምን አመጣን? ማን አመጣልን” የሚል ሰው ሲያጋጥማችሁ፥ ደግሞ “የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲን ታሪክ አንብብ በሉት።

ፕሮፌሰር  ጌታቸው ኃይሌ

 

Prof. Getatchew Haile's full remarks from NYC

Book Event (excerpted above).

ዶክተር አክሊሉ እንደሚለው “የትምህርት ታሪክ የሕዝብ ታሪክ” ሆኖ ሳለ፤የኢትዮጵያ ታሪክ በየገጹ በሚጻፍበት በአሁኑ ጊዜ፤ታሪኩ ሳይጻፍ እስከ ዛሬ መቆየቱ፤ ያስገርማል። አሁንም ዶክተር አክሊሉ ባይነሣና ብዕሩን ባይመዝ ባዶ እጃችንን እንቀር ነበር። እንደተባለው፤ የትምህርት ታሪክ የሀገር ታሪክ ስለሆነ፤ ሀገሩን ለማወቅ ለሚፈልግ ሁሉ የከፍተኛ ትምህርት መቋቋምና መስፋፋት ቀርቦለታል።በውስጡ ላለፈና በተያያዘ ሁኔታ ትምህርትን ላገለገለ ሁሉ፤ ይህ መጽሐፍ  ትራስ ሆኖት የሚኖር ይመስለኛል።                           

                                 ፕሮፌሰር  ጌታቸው ኃይሌ

 

ይህ መጽሐፍ ብዙ እልፍኞች ያሉት ታላቅ አዳራሽ ይመስላል።  የመጽሐፉ መሠረት ብዛትና ጥራት ያላቸው መረጃዎች ስለሆኑ ደራሲውን የሚያኮራ እና አንባቢ የሚያረካ መጸሐፍ እንደሆነ አምናለሁ። ግርማዊ ጃንሆይ ለትምህርት ከሁሉ የበለጠ ትኩረት የሰጡ እንደነበር ይታወቃል። ይህ የሆነበትንም ምክንያት  በማብራራት ጃንሆይ ስለትምህርት የነበራቸውን ግንዛቤና ራዕይ ከዚህ መጽሐፍ ለመረዳት ይቻላል።                    

                                 ዶክተር ሙሉጌታ ወዳጆ

 

ይህ መጽሐፍ የኢትዮጵያን የመጀመርያውንና አሁንም ያለውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት መሠየም እድገትና ሂደት፤ አሁንም እየቀጠለ ያለውን ታሪክ፤ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ ኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ቀደም ሲል ከ1957 - 1969 ዓ.እ. ባስተማሪነትና በዲንነት፤ ቀጥሎም ከ1969-1974 ዓ.እ. በፕሬዚደንትነት ያገለገሉት ዶክተር አክሊሉ ሀብቴ በተሟላ

የምርምር ዘገባና በጠራ አማርኛ ላንባቢ ቀርቧል። መልካም ንባብ። 

                                ፕሮፌሰር  ንጉሤ  አየለ

Notice the new Ethiopic font on our site? 

We are previewing Menbere, a forthcoming font from Art Beteseb,

created by Aleme Tadesse. For information, email catchaleme@gmail.com.

bottom of page